በባሕርዳር ከተማ ለሚገነባው ሰንፔር ጠቅላላ ሆስፒታል በብፁዓን አባቶች ቡራኬ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
በባሕርዳር ከተማ ለሚገነባው ሰንፔር ጠቅላላ ሆስፒታል በብፁዓን አባቶች ቡራኬ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
በርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ አስተባባሪነት ለሚገነባው ሰንፔር ጠቅላላ ሆስፒታል በብፁዓን አባቶች ቡራኬ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ዛሬ በባሕርዳር ከተማ አዲሱ የዓባይ ድልድይ አካባቢ በድምቀት ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ እና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በመገኘት በጸሎትና በቡራኬ የመሠረት ድንጋዩን አስቀምጠዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባሕርዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው፣ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ፣ የባሕርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ፣ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የሁለቱም አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች፣ በርካታ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የጽዋ ማኅበራት አባላትና በርካታ ምእመናን በመገኘት መርሐ ግብሩን አክብረዋል።
በዝግጅቱ ወቅት ሆስፒታሉ ለሕብረተሰቡ ዘመናዊና ተደራሽ የጤና አገልግሎት በመስጠት የሕይወት ማዳን ተልዕኮ እንደሚያከናውን ተገልጿል። ተሳታፊዎችም ፕሮጀክቱ በተጀመረው ፍጥነት ተጠናቆ ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ ያላቸውን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ሰንፔር ጠቅላላ ሆስፒታል ሲጠናቀቅ ለባሕርዳር ከተማ፣ ለአማራ ክልል እንዲሁም ለመላው ሀገር የጤና አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተጠቁሟል።